Another_essay 4(Amharic version)

       

አውደ ድንቁርና

“ለአመት አውድ ፣ ለህይወትም አውድ ፣ ለውሃም አውድ… ግን ለድንቁርናም አውድ አይከብድም?”  እንዳትሉኝ ።   አውድ ድግግሞሽ ወይም (cycle) ማለት አይደል? ስለዚህ አዎ ለድንቁርናም አውድ አለው ባይ ነኝ።
      አንዳንድ ጊዜ ተመክረን እና ተዘክረን አልሰማም ያልነውን እና ለመታረም ፈቃደኛ የማንሆነውን ነገር ጊዜ እራሱ ያስተምረናል። ነገርግን ጊዜው ስለሚያልፍ ከቁጭት ውጪ ምንም ማድረግ አንችልም፥ ያለፈንን እና የምንቆጭበትን ነገር ለታናናሾቻችን ከመምከር ውጪ።
እነርሱም ታዲያ ልክ እኛ በእነሱ እድሜ የታላላቆቻችን ምክር ይሰለቸን እና ሚጨቀጭቁን የመስለን እንደነበረ እኛም በተራችን የምንጨቃጨቅ የምንመስላቸው እንሆናለን ። በትውልዱ ላይ ፈራጅ ደግሞም ተስፋ ቆራጭ እንሆናለን። ከዚያም እነሱም ምክራችንን ንቀው ይተዉት እኛ ያጠፋነውን ጥፋት ይደግሙታል፤ እኛን ያመለጠን እድል ያመልጣቸዋል፤ እኛ የወደቅነውንም ውድቀት ይወድቃሉ። ከዚያም የኛኑ ቁጭት መልሰው ይቆጫሉ። የቀደመውን ትውልድም ይጠላሉ
በስተመጨረሻም ከነሱ በታች ለሚመጣው ትውልድ ከጥፋታቸው ይማር ዘንድ “ምክር” መስጠት ይጀምራሉ።  ታዲያ ይሄ “አውድ” አይደል? 

“ፌዘኛን የሚገስፅ ለራሱ ስድብን ይቀበላል፤ሃጥያንንም የሚዘልፍ ነውርን ያገኛል። ፌዘኛን አትገስፅ እንዳይጠላህ፤ ጠቢብን ገስፅ ይወድህማል። ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፤ጥበብንም ያበዛል። ፃድቅንም አስተምረው፤ እውቀትንም ያበዛል።  …”ምሳሌ 9:7-9

“እናስ ምን ተሻለው ለዚህ ትውልድ?” ያላችሁ እንደሆነ ብቸኛ መፍትሄው ይሄ ነው።

    “…የጥበብ መጀመሪያ እግዚያብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው።”                                          
                                                           ምሳሌ 9:10

          ለዚህ ትውልድ ብቸኛ መፍትሄው እግዚአብሔርን መፍራት መጀመሩ ነው። እግዚአብሔርን በመፍራት ጥበብ ያደገ ትውልድ ከስህተቱ ለመማር ደግሞም ለመታረም ፈቃደኛ ነው። መንገዱን ለማስተካከል እንቢተኛ ያልሆነ አስተዋይም ጭምር ነው። በቅንነት አድምጦ መልካም ምክርን ገንዘቡ ያደርጋል። 

 እግዚአብሔርን በመፍራት ጥበብ ያደገ ትውልድ በደልን ትቶ ይቅር ለማለት አይቸገርም። ይቅር ለማለት ብቻ ሳይሆን ይቅርታ ለመጠየቅም አይቸገርም። ሲያቅተው፣ ሲደክመው እና ሲታክተው፣ ጥበብ እና ማስተዋል ሲጎድለው፣ ትዕግስቱ ሲያልቅ ደግሞም ፍቅር ከውስጡ ጠፍቶ ጥላቻ ሲተካው ፣ግራ ሲገባው እንደሌላው አይቅበዘበዝም። ይንበረከካል።


“ከእናንተ ግን ማንም ጥበብ ቢጎድለው፥ ሳይነቅፍ በልግስና ለሁሉ የሚሰጠውን እግዚአብሔርን ይለምን፥ ለእርሱም ይሰጠዋል።”

     ያዕቆብ1፡5


ስለዚህ የሚመጣውን ትውልድ በምክር መሰል ፍሬ አልባ ንዝንዝ ከምናሰለች አስቀድመን እግዚአብሔርን መፍራት ማስተማር ይበጃል። ያኔ ፍሬ ያለው ንግግር፣ ፍሬ ያለው ህይወትን፣ አካሄድን እና ታሪክን አውርሰን እናልፋለን። አይመስላችሁም?

Popular Posts