ብንሄድ ይሻለናል?

ምን ብዬ ከየቱ እንደምጀምር አላውቅም። በውስጤ የሚመላለሰውን ሃሳብ ለመግለጽ በየትኛው መንገድ ብናገር ይሻል ይሆን ብዬም ብዙ አብሰለሰልኩ። ድምጼን ለመቅረጽ ሞከርኩ። ምን አልባት ሻል ካለ፣ የሰውንም ትኩረት ይዞ መልዕክቴ ከተሰማም ብዬ ምስል ቢጤ ለመቅረጽ ሞከርኩ። ሙከራዎቼ ሁሉ ለራሴው አልጥምም ሲሉኝ እንደልማዴ ሃሳቤን ልጽፈው ወስኜ ከወንበሬ ተሰየምኩ።

 አልነጋም ያሉኝ ሌሊቶቼ፣ ባልነጋ ብዬ የተመኘኋቸው ደግሞ ምሽቶቼ፣  “ጌታ ሆይ ወይ ና፣ ወይ እኔን ውሰደኝ” የሚሉት ጸሎቶቼ፣ መኖር መቀጠል ከብዶኝ ጨለማ ሆኖብኝ ትናንትናዎቼን እያሰብኩ እንባዬን ያፈሰስኩባቸው ቀናቶች ሃሳቤን ሞልተውታል።

ትናንትና የነበረችው ኤደን ዛሬ እንዲህ አይነት ቦታ መድረስ ይቅርና ነገ መንጋቱንም ተጠራጥራለች። የተረሳች፣ ጠያቂ ዘመድ አልባ የሆነች ያህል ተሰምቷታል። ስሟን ጠርቶ የሚፈልጋት ሰው ጥበቃ በመስኮት ሳትታክት ጠብቃለች። ታሪኳ ያበቃ፣ የተዘጋ መዝገብ ሆኖባታል። ነገን ማሰብ ህልም ሳይሆን ቅዠት ሆኖ ፍርሃት ለቆባታል። ትናንትና የነበረችው ኤደን ከገደል አፋፍ ላይ ቆማ ያ ተአምር ሲያደርግ የነበረውን የእስራኤል አምላክ ማዳንን ናፍቃለች። ተማጽናለች፣ አልቅሳለች፣ ወደልቧም አምላክ ጮሃለች።

የትናንትናዋ ኤደን ከሷ አልፎ “ ወይኔ ልጄ ምነው ባልሄድሽብኝ ኖሮ ”  የሚል የእናቷን ንግግር እያስታወስች ሰላሳ የጭንቅ ቀናትን አሳልፋለች። ከመቀመጥ ማሄድ ይሻላልም ብላ ደምድማ ነበር። በገዛ ሰውነቷ ላይ ግን ስልጣን እንደሌላት ታውቅ ነበርና የእሷነቷ ባለቤት እግዜሩ እንዲሰበስባት ትማጸነው ነበር።

ያ ሁሉ አልፎ ግን ያም ታሪክ ሆኖ የአምላኳን ማዳን፣ ድንቅ አደራረጉን ታወራ ዘንድ ወደደች። የማይነጋ የሚመስለው ሌሊት አለፈ። ውሰደኝ ስትለው ወደከበረ ወደተሻለ ስፍራ ወሰዳት። የተረሳች የመሰላትን ቀናቶች አስረስቶ በብዙዎች ፊት ሞገስ ሆናት። እንባዋን ከአይኗ አብሶ አፏን በሳቅ ሞላ። 

ውድ አንባቢዎቼ ሆይ፣ የታሪካችሁ ጸሃፊ እሱ የሁሉ ፈጣሪ ነው። አይሳሳትም። ደግሞም እንዲሁ ያለምክኒያት የምናልፍበት መንገድ ሲከብደን ቸል አይለንም። መወጣት የማንችለው ፈተና ውስጥ አይከተንም። እርሱ ከሃጢያት በቀር በሁሉ ተፈትኗልና የልጆቹን ሁኔታ ይረዳል።

አይዞሽ እህቴ! አይዞህ ወንድሜ! ሰው ሊረዳችሁ ባይችል የልባችሁን የሚረዳ ከእስትንፋሳችሁ የቀረበ ወዳጅ አለችሁና አትዘኑ! ተስፋም አትቁረጡ!

 

“በፈተና የሚጸና ሰው የተባረከ ነው፤ ከተፈተነ በኋላ ለሚወዱት ተስፋ ስለ እርሱ የሰጣቸውን የሕይወትን አክሊል ይቀበላልና።”

  — ያዕቆብ 1፥12

Popular Posts